Amharic: New Testament

World English Bible

2 Corinthians

11

1በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ።
1I wish that you would bear with me in a little foolishness, but indeed you do bear with me.
2በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤
2For I am jealous over you with a godly jealousy. For I married you to one husband, that I might present you as a pure virgin to Christ.
3ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።
3But I am afraid that somehow, as the serpent deceived Eve in his craftiness, so your minds might be corrupted from the simplicity that is in Christ.
4የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።
4For if he who comes preaches another Jesus, whom we did not preach, or if you receive a different spirit, which you did not receive, or a different “good news”, which you did not accept, you put up with that well enough.
5ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም።
5For I reckon that I am not at all behind the very best apostles.
6በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል በነገር ሁሉ ተገልጠንላችኋል።
6But though I am unskilled in speech, yet I am not unskilled in knowledge. No, in every way we have been revealed to you in all things.
7ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን?
7Or did I commit a sin in humbling myself that you might be exalted, because I preached to you God’s Good News free of charge?
8እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ።
8I robbed other assemblies, taking wages from them that I might serve you.
9ከእናንተም ጋር ሳለሁ በጎደለኝ ጊዜ፥ በማንም አልከበድሁበትም፤ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ሰጥተዋልና፤ በነገርም ሁሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ።
9When I was present with you and was in need, I wasn’t a burden on anyone, for the brothers, when they came from Macedonia, supplied the measure of my need. In everything I kept myself from being burdensome to you, and I will continue to do so.
10የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህት በእኔ ዘንድ በአካይያ አገር አይከለከልም።
10As the truth of Christ is in me, no one will stop me from this boasting in the regions of Achaia.
11ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል።
11Why? Because I don’t love you? God knows.
12ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ።
12But what I do, that I will do, that I may cut off occasion from them that desire an occasion, that in which they boast, they may be found even as we.
13እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና።
13For such men are false apostles, deceitful workers, masquerading as Christ’s apostles.
14ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።
14And no wonder, for even Satan masquerades as an angel of light.
15እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
15It is no great thing therefore if his servants also masquerade as servants of righteousness, whose end will be according to their works.
16እንደ ገና እላለሁ። ለማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ ያለዚያ ግን እኔ ደግሞ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ።
16I say again, let no one think me foolish. But if so, yet receive me as foolish, that I also may boast a little.
17እንደዚህ ታምኜ ስመካ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም።
17That which I speak, I don’t speak according to the Lord, but as in foolishness, in this confidence of boasting.
18ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ።
18Seeing that many boast after the flesh, I will also boast.
19ልባሞች ስለምትሆኑ በደስታ ሞኞችን ትታገሣላችሁና፤
19For you bear with the foolish gladly, being wise.
20ማንም ባሪያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበላችሁ፥ ማንም ቢቀማችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁና።
20For you bear with a man, if he brings you into bondage, if he devours you, if he takes you captive, if he exalts himself, if he strikes you on the face.
21ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ።
21I speak by way of disparagement, as though we had been weak. Yet however any is bold (I speak in foolishness), I am bold also.
22ዕብራውያን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የእስራኤል ወገን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን?
22Are they Hebrews? So am I. Are they Israelites? So am I. Are they the seed of Abraham? So am I.
23እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።
23Are they servants of Christ? (I speak as one beside himself) I am more so; in labors more abundantly, in prisons more abundantly, in stripes above measure, in deaths often.
24አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ።
24Five times from the Jews I received forty stripes minus one.
25ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ።
25Three times I was beaten with rods. Once I was stoned. Three times I suffered shipwreck. I have been a night and a day in the deep.
26ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤
26I have been in travels often, perils of rivers, perils of robbers, perils from my countrymen, perils from the Gentiles, perils in the city, perils in the wilderness, perils in the sea, perils among false brothers;
27በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።
27in labor and travail, in watchings often, in hunger and thirst, in fastings often, and in cold and nakedness.
28የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።
28Besides those things that are outside, there is that which presses on me daily, anxiety for all the assemblies.
29የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን?
29Who is weak, and I am not weak? Who is caused to stumble, and I don’t burn with indignation?
30ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ።
30If I must boast, I will boast of the things that concern my weakness.
31ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል።
31The God and Father of the Lord Jesus Christ, he who is blessed forevermore, knows that I don’t lie.
32በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥
32In Damascus the governor under King Aretas guarded the city of the Damascenes desiring to arrest me.
33በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።
33Through a window I was let down in a basket by the wall, and escaped his hands.